የአሰብ ወደብን ከኢትዮጵያ ግዛት ጋር የሚያገናኙ መንገዶች ጥገና በቅርቡ እንደሚጠናቀቅ ተገለጸ

የአሰብና የምፅዋ ወደቦችን ለመጠቀም በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል በተደረገው ስምምነት መሠረት፣ በአራት ኮሪደሮች ሁለቱን አገሮች ከሚያገናኙት መንገዶች ውስጥ በአሰብ መስመር ከዲቼቶ ጋላፊ መገንጠያ እስከ ቡሬ ያለው መንገድ ላይ የተጀመረው ጥገና በቅርቡ እንደሚጠናቀቅ ተገለጸ፡፡
ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ያገኘነው መረጃ እንደሚያስረዳው፣ በአሰብ ከዲቼቶ እስከ ቡሬ ድረስ ባለው መስመር ጥገና እየተደረገለት የሚገኘው መንገድ 71 ኪሎ ሜትር ርዝማኔ ያለው ነው፡፡ መንገዱን በቶሎ ለአገልግሎት ክፍት ለማድረግ የጥገና ሥራው ለኢትዮጵያ መንገድ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን ተሰጥቶት ጥገናው በመካሄድ ላይ ይገኛል።
በጥገና ላይ የሚገኘው መንገድ፣ ግንባታው ቀደም ብሎ ከተጀመረው ከዲቼቶ ጋላፊ መገንጠያ ኤሊደር በልሆ መንገድ ፕሮጀክት ጋር በመገናኘት ለአሰብ ወደብ መዳረሻ የሆነችውን የቡሬ ከተማን ያገናኛል፡፡
የመከላከያ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ ከዲቼቶ ጋላፊ መገንጠያ ኤሊዳር በልሆ ድረስ ያለውን 78 ኪሎ ሜትር መንገድ መገንባት የጀመረው በጥቅምት 2008 ዓ.ም. እንደነበር ይታወሳል፡፡ ከ2.6 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚደረግበት የዚህ መንገድ ግንባታ የተጀመረው የአሰብ ወደብን ለመጠቀም ታስቦ ሳይሆን፣ጂቡቲ ያስገነባችውን የታጁራ ወደብ ታሳቢ በማድረግ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡ አሁን ግን በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል በተደረገው ስምምነት መሠረት አሰብ ወደብን መጠቀም እንደሚቻል በመረጋገጡ፣ ከዚህ ፕሮጀክት 64 ኪሎ ሜትሩ በአሁን ወቅት እየተጠገነ ከሚገኘው 71 ኪሎ ሜትር መንገድ ጋር ተደምሮ ለአሰብ ወደብ አገልግሎት እንዲመቻች ተደርጓል፡፡
በጥገና ላይ ያለው መንገድ ከኢትዮ - ኤርትራ ጦርነት ቀደም ብሎ በሶጃ በተባለ የፈረንሣይ ተቋራጭ እንደተገነባ ታውቋል፡፡ የአሰብን መስመር ለመጠቀም እየተመቻቸ ያለው መንገድ ከአዲስ አበባ - አዋሽ - ሰመራን አልፎ በዲቼቶና በጋላፊ መካከል ወደ ግራ ተገንጥሎ ወደ አሰብ የሚጓዝ ሲሆን፣ በጠቅላላው 882 ኪሎ ሜትር ይሸፍናል፡፡ ከዚህ ውስጥ 71 ኪሎ ሜትር የሚሆነው በኤርትራ ግዛት ውስጥ የሚገኝ ነው፡፡ እንደ መንገዶች ባለሥልጣን መረጃ፣ መንገዱ የበለጠ አገልግሎት እንዲሰጥ ግን እንደ አዲስ መገንባት ይኖርበታል። በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገርናቸው የባለሥልጣኑ ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ወንድሙ፣ ጥገና ተደርጎለት ለአገልግሎት የሚበቃው መንገድ የአገሪቱን የወጪና ገቢ ንግድ በአሰብ ወደብ ለማስጀመር የሚያስችል ሲሆን፣ ወደፊት ግን የመንገዱን ደረጃ ይበልጥ የማሻሻል ሥራ ይሠራል ብለዋል። እንደ አቶ ሳምሶን ገለጻ፣ ወደፊት በአሰብ መስመር ሊኖር የሚችለውን የትራፊክ ፍሰት ሊመጥን የሚችል መንገድ ማስፈለጉን ታሳቢ በማድረግ ይኸው ተጠንቶ ለመንግሥት ጥያቄ ይቀርባል፡፡
ከአሰብ ወደብ ኮሪደር በተጨማሪ፣ ከኤርትራ ጋር የሚያገናኙ ሌሎች መንገዶችም ከድልድይ ግንባታ በስተቀር ከፍተኛ ግንባታ የማያስፈልጋቸው በመሆናቸው፣ ግንባታዎቹን በማካሄድ ለአገልግሎት ዝግጁ ማድረግ እንደሚቻል ባለሥልጣኑ አስታውቋል።
በቅርቡ ከቻይና መልስ ወደ ኤርትራ ያቀኑት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በኤርትራ በኩል የሚዘረጋውን 71 ኪሎ ሜትር የመንገድ ሁኔታ መመልከታቸውና ይሁንታቸውን መስጠታቸው ተዘግቧል።