በሀገሪቱ እየተገነቡ ያሉ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ከ3 ወር በኋላ ተጠናቀው ወደ ስራ ይገባሉ
አዲስ አበባ፣ ህዳር 17፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች እየተገነቡ ያሉ 6 ኢንዱስትሪ ፓርኮች ከ3 ወር በኋላ ተጠናቀው ወደ ስራ ይገባሉ።
በመጀመሪያው ዙር ከተያዙት 11 የኢንዱስትሪ ፓርኮች መካከል አምስቱ ተጠናቀው ስራ የጀመሩ ሲሆን፥ ስድስቱ ደግሞ በያዝነው አመት አጋማሽ ላይ ግምባታቸው ተጠናቆ ወደ አገልግሎት እንደሚገቡ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን መረጃ ያስረዳል።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ዳይሬክተር ወይዘሪት ሌሊሴ ነሜ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት፥ ከሶስት ወር በኋላ ወደ ስራ ይገባሉ ተብለው ከሚጠበቁት የኢንዱስትሪ ፓርኮች መካከል ድሬዳዋ፣ ቦሌ ለሚ፣ ባህር ዳር፣ ጂማ፣ ደብረ ብርሃን እና አረርቲ ይገኙበታል።
እነዚህ ፓርኮች በየአመቱ ከፍተኛ ትምህርት እና ቴክኒክና ሙያ ተቋማት እስከ 600 መቶ ሺህ የሚጠጉ ወጣቶች ተመርቀው ለስራ ዝግጁ እንደሚሆኑ ለሚነገርላት ኢትዮጵያ ለበርካታ ስራ አጥ ወጣቶች ሰፊ የስራ እድል እንደሚፈጥሩም ዳይሬክተሯ ተናግረዋል።
ፓርኮቹ የሚገነቡባቸው አካባቢ ነዋሪዎችን የስራ እድሉ ተጠቃሚ ለማድረግ እና የኑሮ ደረጃቸውን ለማሻሻል እየተሰራ መሆኑንም ነው ዳይሬክተሯ የተናገሩት።
አብዛኛዎቹ ፓርኮች የጨርቃጨርቅ እና አልባሳት ውጤቶችን ታሳቢ በማድረግ እየተገነቡ መሆኑን ያነሱት ዳይሬክተሯ፥ ከአካባቢው አርሶ አደሮች የሚቀርቡ ጥሬ እቃዎች የጥራት ጉዳይ አጠቃቀማቸውን ውስን አድርጎታል ብለዋል።
የግብርና ውጤቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች በክልል የሚመሩ ሲሆን፥ ለወደፊቱ ከአካባቢው አርሶ አደሮች ጋር በቅርበት በመስራት በአካባቢው የሚቀርቡ የግብዓት አቅርቦቶችን ለማሻሻል እንደሚያስችልም ገልጸዋል።
አካባቢያዊ የገበያ ትስስሩን ለማጠናከርም ከ55 የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ ሲሆን፥ ከላይ ከተጠቀሱት ሼዶች ውስጥ ሀገር በቀል ባለሀብቶችም እንዲሳተፉ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
እየተገነቡ ያሉት ሼዶች ከ3 ሺህ እስከ 11 ሺህ ሜትር ስኩዌር ስፋት ሲኖራቸው፥ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን በማሳተፍ ረገድ በሀዋሳ እና አዳማ በጅምር ደረጃ የሚታዩ ስራዎችን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ዳይሬክተሯ አንስተዋል።
ኢትዮጵያን በ2025 መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ ለማሰለፍ በሚደረገው ጥረት ውስጥ እስከ 30 ኢንዱስትሪ ፓርኮች እንደሚገነቡ ይጠበቃል።
ይህም ከ5 እስከ 20 በመቶ የምጣኔ ሀብት ድርሻ እንደሚኖረው ይጠበቃል ተብሏል።