በ2025 ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሆነ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ለመፍጠር እየተሠራ መሆኑ ተገለፀ
አዲስ አበባ፣ ህዳር 18፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ)በ2025 ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሆነ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ለመፍጠር እየተሠራ መሆኑን የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ካሊድ አብዱራህማን አስታወቁ፡፡
የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ቴክኖሎጂ እና ማኔጅመንት ባለሙያዎች ማኅበር ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ከዓለም አቀፍ እና ሀገር አቀፍ የኮንስትራክሽን ዘርፎች ተሞክሮዎችን ለመቅሰም ለ7ኛ ጊዜ ዓለም አቀፍ ወርክሾፕ አዘጋጅቷል፡፡
በዚህ ወቅት የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ካሊድ አብዱራህማን ፥ በኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ እየተስፋፋ እንደሚገኝ የገለፁ ሲሆን፥ ከባለድርሻ አካላት፣ ከዘርፉ ባለሙያዎችና በዓለም አቅፍ ደረጃ ተሞክሮዎችን በመውሰድ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ቴክኖሎጂና ማኔጅመንት ባለሙያዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት እና የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሞገስ ጥበቡ በበኩላቸው፥ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ባለፉት 10 ዓመታት ውስጥ ከፍተኛ እምርታ ማሳየቱን ገልፀዋል።
የሥራ እድል ከመፍጠር ረገድም ከግብርና ቀጥሎ በሁለተኛ ደረጃ የሚገኝና ለሁሉም ኢንዱስትሪዎች ምቹ ሁኔታዎችን የፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ኢንጂነር ሞገስ ጥበቡ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን እድገት ወደ ኋላ የሚጎትቱ ነገሮች እንዳሉ በመግለፅ ስጋቶችን ለመቀነስ የጥራት ቁጥጥር ማድረግ፣እስከታች ድረስ የተጠያቂነት አሠራር መዘርጋት እና ዘመናዊና ዲጂታላይዝ አሠራር መከተል ያስፈልጋል ማለታቸውን ከአዲስ አበባ ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
በተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን አዳራሽ ኢሲኤ በተካሄደው ዓለም አቀፍ ወርክሾፕ ላይ ከእንግሊዝ፣ደቡብ አፍሪካ፣ሲንጋፖርና ሕንድ የመጡ ተወካዮች ተሞክሮዎቻቸውንና ልምዶቻቸውን አቅርበዋል።