የውጭ የሎጂስቲክስ ኩባንያዎች የ49 በመቶ ድርሻ ይዘው እንዲገቡ ተፈቀደ

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ቦርድ ለአገር ውስጥ ባለሀብቶች ብቻ ተከልሎ የቆየውን ዕቃዎችን የማሸግ፣ የማስተላለፍና የመርከብ ውክልና አገልግሎቶችን በመስጠት  መስክ ዓለም አቀፍ የሎጂስቲክስ ኩባንያዎች ከ49 በመቶ በታች ያለውን አናሳ ድርሻ በመያዝ፣ ከአገር ውስጥ የሎጂስቲክስ ኩባንያዎች ጋርበሽርክና እንዲሠሩ ወሰነ፡፡

ቦርዱ በአዋጅ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት የቦንድድ መጋዘን፣ የኮንሶሊዴሽንና ዲኮንሶሊዴሽን የተባሉ አገልግሎቶች ማቅረብን ጨምሮ በሚኒስትሮች ምክርቤት ደንብ ቁጥር 270/2005 (እንደተሻሻለው) ለአገር ውስጥ ባለሀብቶች ብቻ ተከልሎ የነበረውን ዕቃዎችን የማሸግ፣ የማስተላለፍና የመርከብ ውክልናአገልግሎቶችን የመስጠት የኢንቨስትመንት መስክ፣ ዓለም አቀፍ የሎጂስቲክስ ኩባንያዎች ከ49 በመቶ ያላለፈ አናሳ ድርሻ ይዘው ከአገር ውስጥ የሎጂስቲክስኩባንያዎች ጋር በሽርክና አብረው መሥራት እንዲችሉ ውሳኔ አስተላልፏል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ማክሰኞ ነሐሴ 29 ቀን 2010 ዓ.ም. ለሪፖርተር በላከው መግለጫ ይፋ እንዳደረገው፣ የውጭ ኩባንያዎች በአገሪቱ ሎጂስቲክስ ዘርፍ ውስጥ በቀጥታ በኢንቨስትመንት እንዲሳተፉ ተወስኗል፡፡ ውሳኔው የወጪ ንግድ አፈጻጸምን ለማሳደግ የሚያግዝ የፖሊሲ ውሳኔ ስለመሆኑም የኮሚሽኑ መግለጫ ይጠቅሳል፡፡

ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ተኮርና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተለዋዋጭ ከሆነው የሎጂስቲክስ ኢንዱስትሪ ጋር አብራ እንድትጓዝ፣ ዘርፉም ራሱን ችሎ ለአገሪቱ ኢኮኖሚአስተዋጽኦ እንዲያበረክት የሚያስችሉ ማሻሻያዎች በማስፈለጋቸው፣ ዓለም አቀፍ ልምድ ያካበቱ የሎጂስቲክስ ኩባንያዎች ከኢትዮጵያ ኩባንያዎች ጋርበሽርክና እንዲሠሩ  የሚያስችላቸውን ማሻሻያ መደረጉ ተጠቁሟል፡፡ ውሳኔው የአገር ውስጥ ኩባንያዎችን ተወዳዳሪነትና ውሳኔ ሰጪነት አቅም ለማስጠበቅ፣ብሎም የቴክኖሎጂና የልምድ ልውውጥ ላይ ትኩረት አድርገው እንዲሠሩ ለማስቻል የውጭ ባለሀብቶች አናሳ ድርሻ የሚይዙበትና ዘርፉን ለውጭኢንቨስትመንት ክፍት እንዲሆን የሚቻልበት ውሳኔ ተላልፏል፡፡

በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የአምራቹን ዘርፍ ዕድገት ለማፋጠን፣ ኢንቨስትመንት ለመሳብና የወጪ ንግድ አፈጻጸምን በበቂ መጠን ለማሳደግየሎጂስቲክስና የጉምሩክ አሠራሮችን ማሻሻል እንደሚገባ ቢታወቅም፣ እስካሁን በዘርፉ ይህ ነው የሚባል ጉልህ መሻሻል እንዳልታየ የኮሚሽኑ መግለጫ ያትታል፡፡  የኢትዮጵያ የሎጂስቲክስ ኢንዱስትሪና የጉምሩክ ሥርዓት ከዓለም አቀፍ መመዘኛዎች ጋር ሲነፃፀር ዝቅተኛ አፈጻጸም መገኘቱን ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታውሶ፣ ይህንን ለማስተካከልና የአገሪቱን ዕቅዶች በተግባር ለመመንዘር ብሔራዊ የሎጂስቲክስ ስትራቴጂ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ባለፈው ሳምንት መፅደቁንም አክሏል፡፡

ከዚህም በተጨማሪም ዘርፉ ያሉበትን ችግሮች በመለየት የመፍትሔ አቅጣጫዎችን የሚጠቁም ጥናት ከዓለም ባንክ  ጋር በመተባበር በኮሚሽኑ ሲካሄድ መቆየቱ፣ ዘርፉ ካሉበት የተለያዩ ውስንነቶች መካከል የውጭ ባለሀብቶች ተሳትፎ በመገደቡ፣ በኤክስፖርት ማኑፋክቸሪንግ የሥራ ዘርፍና በሌሎች የገቢና ወጪምርቶች ላይ የተሠማሩ ኢንዱስትሪዎች፣ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት ማግኘት እንዳልቻሉ በተደጋጋሚ ሲጠቀስ ቆይቷል፡፡ ዓለም አቀፍ አምራቾች በሌሎች አገሮች ውስጥ በቀላሉ የሚጠቀሙባቸውን አገልግሎቶች በአገር ውስጥ ማግኘት ባለመቻላቸው፣ በዓለም ገበያ ያላቸውን ተወዳዳሪነት እየጎዳእንደሚገኝ ሲገለጽም ቆይቷል፡፡ እንደ ዲኤችኤል፣ ዩፒኤስና መሰል ኩባንያዎች የሚያጓጉዟቸው ጥቅሎችና ልዩ ልዩ ምርቶችን በኢትዮጵያ ለማጓጓዝ እክል ይገጥማቸው እንደነበርም ማሳያዎች አሉ፡፡